የነገደ የዘፈን ግጥሞች የመሰብሰብ ፍቅር ከወሎ ባህል ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ይቻላል። ወሎ እንድሚታወቀው በሙዚቃ ስሙ የገነነ ነው። አራቱም የሙዚቃ ቅኝቶች ከወሎ እንደፈለቁ ይነገራል። ነገደም ውሎ ተወልዶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ አዲስ አበባ እስከመጣ ድረስ ያደገው በዛው በወሎ ባህል ነው። የዘፈን ግጥም መሰበሰብም የጀመረው፣ ገና በልጅነቱ እዛው ወሎ ነው።
አቶ ተገኝ የተሻወርቅ የሚባሉ፣ በኋላ በጃንሆይ ዘመን የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ ያገለገሉ የነነገደ ጎረቤት ነበሩ። አቶ ተገኝ የተሻወርቅ፣ ትምህርት ላይ ከነበሩበት ከአዲስ አበባ ወደ ወሎ ቤተስቦቻቸውን ሊጠይቁ ሲመጡ፣ የሰፈር ልጆች እየሰበሰቡ ግጥም እንዲያመጡላቸው ይጠይቋቸው ነበር። ከግጥም ሰብሳቢዎቹ አንዱ ነገደ ነበር። አቶ ተገኝ ፣ እሳቸው የሌላቸውን ግጥም ላመጣ ልጅ 10 ወይም 15 ሳንቲም ይሰጡ ነበር። በዚህም የባህላዊ ዘፈኖች ግጥም የመሰብሰብ ባህል ለነገደ ከልጅነት ጀምሮ የዘለቀ ሆነ። የሚያውቀውን ሰው የዘፈን ግጥም እየጠየቀ የሌለውን መመዝገቡን ገፋበት።
በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር፣ ከስብሰባ በሁዋላ ማታ ማታ እየተቀባበሉ መዝፈን የተለመደ መዝናኛ ነበር። ነገደም በዚህ “ፕሮግራም » ከግጥምና ዘፈን አውራጆች አንዱ ነበር።
Poetry
ግጥም
ነገደ ጎበዜ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የግጥም ውድድር በፕሬዜንዳንቱ የተሸለምኩበትና ኮሌጅ ደይ የተነበበ
1955 ዓ.ም
በአለፈው ሰሞን ነው ቅዳሜ ለት ማታ
የኔ ልጅ ደግሶ
ጓደኞቹን ሆሉ ከየትም ከየትም
በሙሉ አግበስብሶ
እንደ አባትነቴ እኔም ተጠርቼ
ብዙ ጉድ አየሁኝ ብዙ ተመለከትሁ
አዳምጡኝ ልጆቼ
ገብቼ ቁጭ እንዳልኩ ልጄን ጠራሁና
በል እስቲ ፅዋውን ወዲህ አምጣው ልጄ ልሳለመውና…
አልኩና ስጀምር ከት ብሎ ሳቀ
እኔም ወዲያውኑ መሳሳቴ ገባኝ
ህሊናየ አወቀ
ወዲያውኑ ልጄም መንከትከቱን ትቶ
ፓርቲ ነው ፕርቲ ነው?
ብቻ ስሙን እንጃ አላውቀውም ከቶ
የሚባል ጠበል ነው አሁን የምንጠጣው ልንገርህ አባባ
እዚሁ ቁጭ ብለህ ሁሉንም ተመልከት ወደ ውስጥ አትግባ
ፅዋ እሚሉ ነገር የለም እዚህ ቦታ
ብዙ ጉድ ታያለህ ይህ ልዩ ነገር ነው አይዞህ ዛሬ ማታ
ምንም አልመለስኩም በጣም አፈርኩና
“እሺ” ብቻ ብየው ሄደ ከአጠገቤ ቶሎ ተነሳና።
ወዲያው እንግዶቹ አንድ በአንድ እያሉ
ሴቶች ከወደፊት ወንድ እያስከተሉ
ይገቡ ጀመረ ምን ምን የመሰሉ
ሰው መግባት ሲጀምር ሊጋበዝ ሊበላ
አንዲቷ ልበ ውልቅ እያረገረገች እየሳቀች ገባች
የፈረደበትን ወንዱን አስከትላ
እኔም አስገርሞኝ የአለባበሷና የአኳሆኗ ነገር
ምን ከርፋፋ ነች ይች ሴት አሰዳቢ ምን ያስች ባላገር
ልቧ የት ሄዶ ነው እንደዚህ አድርጋ ራሷን መርሳቷ
ቢጠፋ ቢጠፋ የእናት ኩታ እያለ የአባት ጋቢ እያለ መጣሉ ደረቷ
ራቁቷን ሆና አሁን በዚህ በብርድ እንዲህ መመታቷ
እንደ በረሃ ጂን ለምን ፀጉሯ ቆመ እረ ለምንድን ነው አለመበጀቱ
እባካችሁ ሰዎች ጤና አኮ አይደለችም አብዳለች ልጂቱ
ወፍጮስ እንደ ዋለች አረ ለምንድን ነው ቀጥታ መምጣቷ
ዱቄቱ እንዳለ ነው ምንም አልተነሳም አልታጠበም ፊቷ
ልበ ውልቅነቷ መች እዚህ ላይ ቆመ አለ ትልቅ ነገር በጣም የተረሳ
እጅዋን አልታጠበች አፏን አልታጠበች በልታ ስትጨርስ ዝበታ ሲነሳ
እከንፈሮቿ ላይ የጎንደር አዋዜ ተለድፎባታል
ደም ሰርቃ የላሰች የመንደር ልክስክስ ውሻ አስመስሏታል
እጅዋም እንዲሁ ነው አልታጠበችውም ጣቷ ተጨማልቋል
ከወገቧም በታች የሁለት ሰው ቦታ አስፋፍታ ይዛለች
ከጉልበቷም በታች ምንም ነገር የላት እንዲሁ ባዶ ነች
ይህስ የችግር ነው እኔ እንደመሰለኝ የእናቷን ተውሳ
ሳይሆን እኮ አይቀርም- ቀሚሷ መስፋቱ እንዲህ ያለ መሳ
ግን ደሞ የእናቷ እንዲህ አያጥራትም አይመስለኝም ከቶ
ከሰፊው ይሆናል ቁራጭ ጨርቅ ሰጥታው እንዲህ አበላሸቶ
በጨለማ ሰጥቷት በችኮላ አጥልቃ ይሆናል መምጣቷ
ወደዚህ በሩጫ እንዲህ ልቧ ወልቆ እየታየ ባቷ
ሰፊው ግን አጥፍቷል እንዲህ ከማስፋት
ትንሽ ጠበብ አርጎ ትንሽ ከቁመቱ ቢጨምርበት
“አጥታ ነው ቸግሯት ድሃ ነች የላትም የሚል ማን ነበረ ይቺን እመቤት?
ደሞስ ለምንድን ነው በነጠላ ጫማ እንዲህ መወጣቱ
ተረከዝዋ እንደሆን የሚሸፈን ነበር ምነው መታየቱ
ወይ እንደለመደች ረስታው ይሆናል የቀየረች መስሏት
ወይኔ ተዋረደች አፈር ይብላኝ ልጄ ዛሬስ አጋለጣት
ምን ያለች ጎደሎ ከሁሱ የጎዳት
ምነው ባትወጣስ ከእናቷ ጋር ብትቆይ ይኸ ቢቀርባት
ከሁሉ እሚገርመው እሷን ሰው ነች ብሎ እየተጎተተ
የወንዱ መከተል አይ የኛ ሞጋጋ ምን ሃሞት የሌለው በፍፁም የሞተ
ሌሎች እስኪገቡ መጠበቅ አልቻልኩም ወጣሁ ተነስቼ
በዚች በወጣት ልጅ እንደዚህ መታመም ልቤን ተመትቼ።
ወዲያውኑ ልጄን እውጭ አስጠርቼ
ምነው ምን ሆናችሁ በሸተኛዋን ልጅ መልሷት እቤቷ
ይሰጉ ይሆናል የት ደረሰች ብለው እናትና አባቷ
ወይንም ነገሯት ቀሚሷን ትቀይር ፊቷን ትታጠበው
ጫማዋም ይለወጥ ፀጉሯን ታበጥረው
በእንዲህ ያለ ቦታ በእንዲህ አይነት ምሸት ሴቶች መምጣታቸው
እረ ለምንድን ነው እንዴትስ ዝም አሉ እናት አባታቸው?
ብዙ አልተናገርኩም የልቤን አውጥቼ ከቶ አልሆነልኝም
አሁንም መልሶ አፌን መቃኛ ልጄ አላናገረኝም
አስረድቶኝ ሄደ ነገሩን በሙሉ
የቀሚስን መርጠር የእንዲያም መንቧለሉ
የፊቷንም ዱቄት የጫማውን ሁሉ
የአፏም ላይ አዋዜ የጎንደር አይደለም የአውሮፓ ነው አሉ!
አስረዳኝ ደህና አርጎ ከታች እስከ ላይ
እንዲህ ማስፈራሪያ ሆና ስትታይ
ፋሽን ነው ይለኛል እኔ ታዲያ ይኸ ይገባኛል ወይ?
ግን ድሃ አይደለችም በሸታም አልያዛት ገባኝ ብልሃቲ
ዱቄትም ብዙ አላት የሆዷ ሞልቶላት ተርፏታል ለፊቷ
አዋዜውም ቢሆን የመጣው ከአውሮፓ፣ እሷ አልሰራችውም አልደከመችበት
ታዲያ ምን ቸገራት የዛሬ ልጅ እንደሁ አትወቅጥ አታምስ እንደዚህ አድርጋ ብትጫወትበት
ግን እኔ ያልገባኝ ፈንጣጣ አስቸግራን ሲገኝ መድሃኒቲ
ምን ነካት ላጃችን ክትባት መጥላቷ
ይህን ሳሰላስል ብቻየን ቁጭ በየ ከጠርሙሴ ጋራ
ከወደቤት በኩል ውካታ ቢበዛ ተነሳሁ ላጣራ
ገና በሩ ስደርስ ሰው ሁሉ ተሳክሮ አለቅጥ ጠጥቶ
እዚያ ያለ ሁሉ ወጣት ሽማግሌ ወንዱ ሴቱ ሳይቀር ጭራሽ ነፍሱን ስቶ
ግብ ግብ ገጥሟል ጠብ ይዟል አምርሮ፣ ደስታውን ረስቶት ጨዋታውን ትቶ
እኔ የገረመኝ የሴቷ ድፍረት ነው ወንዱን ተያይዛ
ና ውደቅ ና ተነስ ስትለው አየሁኝ ማጅራቱን ይዛ
ወንድ መቸም የዋህ ማምረሯ አልገባውም ወገቧን ጨብጦ
ዝም ብሎ ይስቃል ሴት ስለያዘችው በሃፍረት ተውጦ
አንዳንዱስ እንጃለት ይለምናል መሰል ልቀቂኝ እያለ
አዘናግቶ ሊያመልጥ በመልካም ፈገግታ አይን አይኗን ያያታል መስሎት ያታለለ
መታገሉ ላይቀር መጣላቱ ላይቀር ከወንድ ቢጣላ
ይሻል እኮ ነበር እንደዚህ አድርጎ ከሚዋረድ ኋላ
እግሩን ወዲያ ወዲህ መጀሌ እንደያው ከማፈራገጥ
ጥንቱንስ ባይጠጣ ለሴት ፊት ባያሳይ አርፎ ቢቀመጥ
አይሻልም ነበር ከዚህ ሁሉ ማጥ
ወኔየ ተነሳ እኔም ደሜ ፈላ ኩታየን አውርጀ
ከጠቡ መሃከል ደቂቃ አልቆየሁም ጉብ አልኩበት ሄጄ
ወንድ ወንዱን ጠመድኩት እኔ እኮ ወንድ ነኝ ሴቷን ማን ይነካል
ግን የልቤ ሳይደርስ ልጄ መጥት ያዘኝ አስወጣኝ ከመሃል
ጠቡም ሁሉ ቆመ ሰው ሁሉ ወደኔ ይመለት ጀመር
እንዲህ ያለች ጎበዝ ወንድ ነች አያለ ነፍጠኛ ባላገር
ልጄም ይዞኝ ወጥቶ እቅድሟ ቦታ
አባባ ላስረዳህ ጠብ እኮ አልነበረም ያ ሁሉ ውካታ
ዳንስ የሚሉት ዘፈን የፈረንጅ እስክታ
ነውና እባክህን ገብተህ ቁጭ በልና ተመልከት በእርጋታ ።
ገባሁኝ ቁጭ አልኩኝ አዛች አወንበራ መከረኛ ቦታ
ስንቱን አሳየችኝ በዚች ሰአት አድሜ ይኸው ዛሬ ማታ
ማድነቅም ጀመርኩኝ ይህ ዳንስ የሚሱትን የፈረንጅ እስክታ
ተቃቅፈው ደስ ብሏት እያረገረገች አንዲህ በፈገግታ
ካስደገፈች ወዲያ ሁለቱን ጡቶቿን እደረቱ አምጥታ
የለም ማለፊያ ነው እንዲህ አርጎም የለ አየ ጉድ ጨዋታ!
ትከሻውን ይዛው ወገቧን ጨብጦ እያሽኮረመማት
ጨወታ ነው ይላል እኔ መቼ አጣሁት ይህን ሁሉ ብልሃት
ትልቅ ጉድ ፈላ እንጂ እንግዲህ ምን ቀረ አቅፏት ከአቀፈችው
ያለ ሸማግሌ እናቷ ሳትሰማ ያለ ነገር አባት እሷው ጨረሰችው
ያልታደለች እናት ልጅ አለችኝ ብላ
ያልታደሰች እናት አድራለሁ ብላ
ሰርግ ታስባለች ድግስ ታስባለች እቤቷ ቁጭ ብላ
አኔ አየሁት እንጂ እሷ መች ነበረች ጉዳዩ ሲፈፀም ትልቅ ጉድ ሲፈላ!’
አሁንስ ይበቃል ከእንግዲህስ ጉዱን አትስሙት ልጆቼ
እኔስ ብዙ ነበር የተመለከትኩት እግዚአብሄር ይማረኝ
እርሜን ለአንዲት ማታ አጉል ቦታ አምሽቼ!!
ነገደ ጎበዜ
አ.ኢዩ.ኮ
1955 አ.ም.
በይ ብዕሬ ምንላርግ አትበይ
ግጠሚ፤ አትች ተች
እኝኝ በይ ወትውች
ለማን ብለሽ ብእሬ
ካሰኘሽ ምላስ አውጭ
ምን ቸገረሽ ብእሬ
ተርቺ፣ ተርቢ አሽሟጭ
በይ ካለሽ
ልክ ልኩን ንገሪልኝ
ቀንድ ቀንዱን ስበሪልኝ
በይ ተዋጊ ብእሬ
ግጠሚ፤አትቺ ተቺ
ተርቢ፤አሽሟጪ ተርቺ
ብቻ
ለእውነት ለፍትህ ሙቺ
አድር ባይ አተላን አጋልጪ
ብቻ
ለእውነት በእውነት ቆመሸ
ለፍትህ ለነፃነት ለህዝብ ብለሸ
ተናገሪ
ወዳጅ እንዲሰማ አርገሽ
ተዋጊ
ጠላት እንዲሰማው አርገሽ
አይደብርሽ ብእሬ
እቅጩን ሲጠይቁሸ
ሃይል ቃል ጨምሪበት
ምንአለበት
ለፍትህ ለነፃነት
መትከኔ ይታይበት
ንገሪው!
አስከሚገባው ድረስ
አልሰሜ ሁሉ እስኪሰማ
ያልነቃው ሁሉ እስኪነሳ
« ፎቼ ጉድ »
እንዲህ ኖሯል ወይ እስኪል
አርማውን እስኪያነሳ
ንገሪው!
« ያኛውንም »
እጅ እጅ እስኪለው ድረስ
ባፍንጫው እስኪወጣ
ኢምንትነቱን እስኪያውቅ
መፈጠሩን እስኪጠላ
ከትግሉ መድረክ አስኪወጣ!
አወን! በይ ሂጂ ብእሬ አትፍሪ
ባሻሽ እንዳሻሽ አርገሽ
ለወደቁት ጓዶች ብለሽ
ስለ ፍትህ ስለእውነት
ያስሸን ተናገሪ
በይ ብእሬ
ማንን አትበይ
አወን_እሱን_ሰርጎ ገቡን
ያኔ ያንን ጓድ ስንቀብር
አርማውን አንስቻለሁ ያለውን
ከኛ ጋር ግራ እጁን አንስቶ
« እንበቀላለን » የወጣን
ኋላ ከቀብር ተመልሰን
ጓዶችን ለጠላት ሲያስማማ
እጅ ከፍንጅ የያዝነውን
አወን ልክ ነሸ ብእሬ
እሱን ሰርጎ ገቡን!
ዛሬ ደሞ ያች ጓዲት ሞታን
እንደገና ሰርጎን የገባውን
ጥንብ ያንሳውና
አርማውን
« አነሳለሁ » ነው?
ምናምን የወጣውን
እንደገና ከኛ ጋር
ግራ እጁን የቃጣውን
አወን ብእሬ ልክ ነሽ
እሱን_ሰርጎ ገቡን!
የቱን አትበይ ብእሬሞልቷል
ያውልሽ ደግሞ ያኛውን
አወን ወዲያ እነሱ ጋር
ሹክክ ብሎ የቆመውን
ከሃዲውን!
ትላንት እኛ ስናጠቃ
ቀይ ሽብር ነኝ እያለ
« በስተግንባር » ተመስሎ
ያዙኝ ልቀቁኝ ያለውን
ዛሬ እኛ ስንጠቃ
በወዲያ በኩል የቆመውን
አወን ልክ ነሸ ብእሬ
እሱን ከሃዲውን
ጥቀሽለት
ያኔ ያ ከሃዲ ብእሩ
አዳልጦት የፃፈውን
አስታውሺው
ያኔ እዚያ አደባባይ ላይ
ስንፈክር
አብሮን የፈከረውን
ስንማማል
አብሮን ያስተጋባውን
እሳይው
ርቀቱን ልዩነቱን
የዛሬውንና የትላንቱን
ክህደቱን
ከዚያማ ተይው ልቀቂው
ምን ቸገረሽ
አለ የጓዲቶች አጥንት
እሾህ ሆኖ ይወጋዋል
አለ የጓዶቻችን ደም
ጎርፍ ሆኖ ይወስደዋል
አለ የሰፊው ህዝብ ክንድ
ዶግ አመድ ያደርገዋል
አንቺ ብቻ
ጥቀሽ አጣቅሺ አመሳክሪ
ከልፈፋው እስከ ድርጊቱ ያለውን ተናገሪ
አመሳክሪ
የዛሬውን የትላንቱን ክህደቱን
አጋልጭው! አወን እሱን ከሃዲውን
የቱን አትበይ ብእሬ
እንዳፈር ነው
እሱን
አጎንሽ አፍንጫሽ ስር የቆመውን
ደፋሩን
ያን ሃቀኛ ጓዳችንን ደገፍ ብሎ የቆመውን
አወን እሱን
አስመሳዩን አድርባዩን
በሃረግ ቅጥልጥል አስማት
በቃላት ድንፋታ ብርታት
« ዛሬም » እያለ
ዛር ያንደፋድፈውና
ዛሬም
« አለሁ » ብሎ ሊያስመስል
« ዛሬም »
እናንተ ጋ ነኝ ብሎ ሊምል
ግቢ ነፍስ ውጭ ላይ ያለውን
አወን እሱን ብእሬ
አስመሳዩን አድር ባዩን!
አጋልጧ
ትላንት እንደዚያ የጠራ ሰው
ዛሬ ምላሱ ቢተሳሰር
« ከነሱ » ሰፈር ቆሞ
« ግራ » ቋንቋ ቢናገር
አጋልጪ! ምን አስፈራሽ ብእሬ
ተርጉሚ ምላሱን እያፍታታሽ
ቋንቋውን እያጣራሽ
አዋርጂው!
ይቺቺ ክህደት_
ይቺቺ ቅጥፈት
ይቺቺ አድርባይነት እያልሽ
እና ጥቢው
ያኔ ሌላ አሁን ሌላ እያልሽ
አጋልጧ
እንቆቅልሹን ፍቺ
ልዩነቱን አመልክቺ
አወን ብእሬ
እሱን ከጎንሽ የቆመውን
ያንን ጓዳችንን
ደገፍ ብሎ ያረፈውን
አወን ብአሬ
እሱን ደፋሩን አስመሳዩን አድርባዩን!
እንዴት አትበይ ብእሬ
እንዳሻሽ እንዳመቸሽ
ህቡእ ገብተሽ ይፋ ወጥተሽ
ሰማይ ወጥተሽ ምድር ገብተሸ
አይታክትሸ ብእሬ
ብቻ አስተምሪ አጋልጭ
አወን! አይታክትሽ ብእሬ
ሰርጎ ገቡን አናጥቢ
አስመሳዩን አንጓይ
ከሃዲውን አስተፊ
አወን አይታክችሽ ብእሬ
ግጠሚ አትቺ ተቺ
ተርቢ አሽሟጪ ተርቺ
ህቡእ ግቢ ይፋ ውጪ
ብቻ!
አስተምሪ አጋልጧ
ብቻ
ፍትህ ነፃነት ላልነው
የጓዶችን አርማ ላነሳነው
ለአንዲት ኢትዮዽያ ልጆች
ለዚች ምድር ታጋዮች
ብርሃን ጥራትን አምጪ!!
ነገደ ጎበዜ
ኤደን / ደቡብ የመን
ጥቅምት 1970 ዓ.ም
እንዳመቻት የምትወጣ ነፃ ጋዜጣ
ሽሙጥ ዜና አገልግሎት (ሸዜናአ) ዴሞክራሲ ለጭቁኖች ያለገደብ፣ ባስቸኳይ፣ አሁኑኑ… ሲል የቆየው ታጋይሁሉ ከዚህ የትግል መድረክ ከወረደ በኋላ ክህደቱን ለመሸፈን አዳዲስ መፈክሮች አፈለስፋለሁ እያለ ምላሱ ይቆላለፍበት ጀምሯል። አዲሱ የጊዜው መፈክር »ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለጭቁኖች ያለገደብ በትግላችን!’ የሚል ነው።
አዲሱ መፈክር እንደተሰማ በሽሙጥ ዝግጅት ክፍል አካባቢ ትንሽ ውዥንብር መፍጠሩ አይቀሬ ነበር። ከዚያማ ሽሙጥ ያለፉትን ሶስት አመታት ጉዞ ዘወር ብላ ስትቃኝ እውነትም በተለይ ከየካቲት 1966 ኢም. ወዲህ የተጧጧፈየልመና ወቅት ውስጥ ገብተን እንደነበር ተረዳች። ሸሙጥ ይህ ነገር እንደተገለፀላት ወዲያውኑ የትጥል ስልት ለውጥአድርጋለች። እሰከዛፊ እንደምታደርገው እያሽሟጠጠች መለመንን ትታ ለትግል ቅድሚያ በመስጠት እየታገለች ማሸሟጠጥን መርጣለች። ለማንኛውም የዚችን ዴሞክራሲ በትግላችን የምትል አዲስ መፈክር ታሪክ ሪፖርተራችን በትግል ስልት አራማጆች ማለትም በሰደድ፣ ማሌሪድና ወዝ ሊግ አካባቢ ሰርጎ ገብቶ ባጠናቀረው ሪፖርት በመመርኮዝ ያቀረበልንን ሰነድ እንደሚከተለው እናቀርባለን።
አይ አልበዛም ……………ዴሞክራሲስ በትግላችን!
አብዮት አብዮት ብለን ወደ ፈጣሪያችን አዝነን
ስንት አመት ሙሉ ፆመን…ስንት አመት ሙሉ ፀልየን
ቸሩ ፈጣሪያችን ሰምቶአብዮታችን ፈንድቶ
ይኸው ታዲያ የካቲት ላይ አገኘን
አብዮት አብዮት ብለን ለምነን!
ከዚያስ
ከዚያማ ስድስት ወር ሱባኤ ገብተን
ንጉሰ ነገስቱን ተማጥነን
ሃይለ ስላሴ እግር ስር ወድቀን
በፈጣሪ ይውረዱልን ብለን ለምነን
እሳቸውም አዝነው፣ አዝነው፣ አዝነው
ምስኪኖች ! ያውላችሁ አትጨቅጭቁኝ ብለው
ብቻ እዚች ላይ ዙፋኑ
በስተግራ ተሰብሯል ከጎኑ
ስትቀመጡበት አትዝናኑ
ብለው ያውም ምክር ሁሉ ለግሰው
ቤት ያፈራው ነው ብለው
ትራስ ስር ከነበረው
መቋቋሚያ ገንዘብ ትተው
ልመናችንን ሰምተው አከውልን
በርህራሄ ከዙፋን ወረዱልን!
ከዚያስ?
ከዚያማ አርሶ አደሩ ሁሉ ነቅቶ
ወደ ፈጣሪው ይዘን ተደራጅቶ
ተብሎ…60 ሽህ ወጣት ዘምቶ
ድሃው ሁሉ በያለበት ከወጣቱ ጋር ሆኖ
ወደ ፈጣሪው አዝኖ፣ አዝኖ፣ ለምኖ
ምድረ ባለርስት ሁላ
ከጢሰኛው ጋር ሆኖ
እሱም በበኩሉ ባለፈው በሰራው አዝኖ
በሉ እሺ ይሁንላችሁ ያውና
ከናንተ አይብስ ብኝምና
ብሎ ፈቅዶልን
መሬት ላራሹ ሆኖ
ነፃ ወጣን ባለርስት ተለምኖ
ከዚያስ?
ከዚያማ መኪና ለምነን
ወደ ከተማ መጥተን
“በግዜር ትርፍ ቤት ያለህ ና ወዲህ በለኝ ብለን
ዞረን፣ ዞረን፣ ዞረን፣ ዞረን
አምስት ወር ሙሉ ተንከራተን
ይህንን ነገር የወሬ ወሬ
ትርፍ ቤት ያለው ሁሉ ሰምቶ
እንዴት ብቻየን ይህን ሁሉ
ብሎ አዝኖ ተፀፅቶ
እሱም እንደ ባለርስት
በሉ ከናንተ አይብስ ብኝም ብሎ
« ኑ ውሰዱ ያው ትርፍ ቤት » ተብለን
እንዲህ ሆኖ ቤት አገኘን ለምነን!
ከዚያስ?
ከዚያማ እረ ስንቱ ስንቱ!
ብቻ እኛ ለምንን ባገኘነው
የምቀናው ብዛቱ
ኢህአፓና ኢዲዩ
እንደኛ መለመናቸውን ትተው
እኛ ለምነን ባገኘነው
በምቀኝነት ተነሳስተው
ቢያስቸኖሩን፣ ቢቸግረን
አውግዘን፣ አውግዘን፣ አውግዘን
« እንዴ እንዴት ነው? አስታግስልን እንጂ » ብለን
መልሰን ወደ ፈጣሪያችን አዝነን
ወደኋላማ እንዲያውም ጭክን ብለን
« አውድማቸው! » ብለን ፈጣሪያችንን ተማጥነን
ያው ብን አሉልን ደስ አለን
እረ ስንቱ ስንቱ!
ሶስት አመት ልመና ስንት አሳየን!
ከዚያስ?
ከዚያማ አብዮት አገኘንና፣ መሬት አገኘንና
ቤት ንብረታችን ተሟልቶ ምቀኞቻችን ተነና
ይኸ ሁሱ ልብ አርጉ በልመና
አንድ ቀን ቁጭ ብለን ስናወራ
ቅንጦት አማረንና
እስቲ ደሞ ምን እንለምን ?
አልንና
አስበን…አስበን አስበን
« እስቲ ዴሞክራሲ እንለምን » ብለን
ዴሞክራሲ መለመን እንደ ጀመርን
« አቤት ልመና መሰልቸቱ ሁሌ የሰው እጅ ማየቱ »
አልንና
ታክቲክ እንለውጥ ብለን
አዲስ ታክቲክ
ፈልገን፣ ፈልገን፣ ፈልገን
አዲስ መፈክር እምቢ ቢለን
እንደገና ወደ ፈጣሪያችን አዝነን
« አባክህ ፈጣሪ በፈጠረህ…አዲስ መፈክር » ብለን
ለምነን…ለምነን…ለምነን
ሰማይ ቤት ተሰምቶ ፀሎታችን
አዲስ መፈክሮ ወረደ ካምላካችን
« አይ አልበዛም ዴሞክራሲስ በትግላችን! »
የሚል መፈክር ተቀብለን
ያውላችሁ ይህን ይዛችሁ
ለምኑ » ተብለን
እሰይ! እኛም ስልት ለወጥን
ታድለን!!!!
ልመናችን ተሰምቷል! እናሸንፋለን!!
ነጎ ኤደን ደቡብ የመን ጥቅምት 1970 አ.ም.
እናት አገር ? አባት አገር ?
ድሮ ድሮ በልጅነት
ወሎች
የአዱኛን ነገር በቀላሉ
እያነሱ እየጣሉ
በዘፈኑም በተረቱም
በቀልዱም በምሬቱም
የኑሮን ሀሁ ሲያስቆጥሩኝ
አባቴ ነው በቀላሉ
ብዙ ነገር ያብራራልኝ
“እየው ልጄ”
ጽዋው ሞልቶ
ዙሪያውን ፈሶ ምታየው
ኣይምሰልህ ውሃ አይደለም
ያገራችን ድሃ እንባ ነው
ኣይምሰልህ ልክ አይደለም
ፍጡር ቀርቶ
ፈጣሪን ሚያሳዝን ነው »
እያለ አባቴ ነው
“ልክ አይደለም” የምትል
አልባሌ ምትመስል
ከባድ ቃል ያስጨበጠኝ፡፡
ውሃን ከእንባ ሳልቸገር
እንድለይ ያስተማረኝ
አባቴ ነው “ለዚች አገር
“ልክ አይደለም”
ማለት ድፈር” ያለኝ
ታዲያ እንዲህ ሆኖ ነገሩ
“ኢትዮጵያን እናት አገር ብቻ” ቢሉ አልስማማም
እንዴት ብዬ እስማማለሁ?
“ልክ አይደለም” እላለሁ
“ይቺ አገሬ አባት አገሬም ናት” እላለሁ
“ምረጥ ሁለት ወዶ አይሆንም” ቢሉኝ
ግድየለም ጤና ሰው አይበሉኝ
ሁለቱንም እመርጣለሁ
“ኢትዮጵያ እናት አገሬ አባት አገሬም ናት” እላለሁ፡፡
ኋላ ብዙ ቆይቶ
አባቴ መተንፈሻ አሳጥቶ
“ዋ እናንተ ልጆች ወዮላችሁ
ዋዛ ፈዛዛ አበዛችሁ
በርቱ እንጂ ላገራችሁ
“ትጉ ተማሩ” ሲል ተምሬ
“ሰው ሁኑ” ሲል
ሰው ለመሆን ሞክሬ
ከአባቴ ጋር ነው
“ልክ አይደለም” የተባለው
ልክ እንዲሆን የታገልነው
በቀልዱም በአኗኗሩ
በተግሳጽም በምክሩ
የአባት ክብሩ ሳያጥረን
ሲያሻን እኩል ቤት ገብተን
ተከራክረን ተመላልሰን
ከአባቴ ጋር ነው
“ልክ አይደለም” እያልን የቀጠልነው
ታዲያ
የፈሰሰው ሳይታፈስ
ጽዋው
በአናት በአናት ሲፈስ
ፍትሁ
አነሰ ሲሉት ሲቀነስ
ትግሎ
ረዥም ያልነው ሲንዛዛ
ውጣ ውረዱ ሲበዛ
የልጅ እዳ ወደ አባት ሲያልፍ
የልጅ ጣጣ ለእናት ሲተርፍ
አባቴ ነው
“ለማን ብለህ ?ለምን ብለን ? ማለት ትቶ
በነብር ጅራት ተረት
ነጋ ጠባ ወትውቶ
አባቴ ነው
በዓላማ መጽናት ያስተማረኝ
“ለዚች አገር
እስከዳር” ብሎ የመከረኝ፡፡
ታዲያ እንዲህ ሆኖ ነገሩ
“ኢትዮጵያን እናት አገር ብቻ » ቢሉ
አልሰማምም
እንዴት ብዬ እስማማለሁ?
“ልክ አይደለም እላለሁ
“ይቺ አገሬ አባት አገሬም ናት » እላለሁ
“ምረጥ ሁለት ወዶ አይሆንም” ቢሉኝ
ግድየለም ጤና ሰው አይበሉኝ
ሁለቱንም እመርጣለሁ
“ኢትዮጵያ እናት አገሬ
አባት አገሬም ናት » እላለሁ
ግንቦት1992
ከልጃቸው ከዶ/ር ነገደ ጎበዜ
አብዮትን ያህል ዳገት
ቅልበሳን ያህል ቁልቁለት
የአርባ ስንት አመት ፈተና
ደከመህ መሰል ይሁና!
ሙሴ ወዳጄ ምነው?
ግን እኮ ነበር መሃላ
ከድል በመለስ ወደኋላ
ሳንል እስከ ዳር ልንገፋ
ለማን ጥለኸን ትጠፋ?
ሙሌ ወዳጄ ምነው፤
ጓዶች ጓዲቶች ያኔ ሲያልፉ
ከጥራ ከተኝ ሲረግፉ
ይድረስ ለታጋይ መልእክታችን
ምን ይል ነበረ ዜማችን
ሙሴ ወዳጄ ምነው
ገና ስንት ሌሎች ይሰዋሱ
በሌላ ታጋይ ይተካሉ
በኒያ ሰማእታት የትጘል ፋና
ህዝብ እስኪበቃ ለድሉ
ሙሌ ወዳጄ ምነው
ህዝብ ተርቧል እንቢ ለእኔ
ህዝብ ተጠምቷል ኑሮ ምኔ
በቃኝ ከሚሉ ኩነኔ
እንቀጥል ነበር ያልነው ያኔ
ሙሌ ወዳጀ ምነው?
ጓዶች ጓዲቶች አለንና
አይቆምም ትግሉ ተፅናና
እንቀጥላለን አሁንም
እንት ምሰሱዋችን ባትኖርም።
ሙሌ ወዳጄ ምነው
ትግሉ መራር ነው ተባብለን
ላናፈገፍግ ተማምለን
ስንት እየገበሮን ተቋቁመን
ከዚያማ ወዲህ ስንት አየን
ሙሴ ወዳጄ ምነው?
አብዮትን ያህል ዳገት
ቅልበሳን ያህል ቁልቁለት
የአርባ ስንት አመት ፈተና
ደከመህ መሰል ይሁና!
ተንሱ እናንት የረሃብ እስረኞች፣
ፍትህን ስሟት ትጮሃልች፣
ባህር ውቅያኖስ ተራራ፣
አቋርጣ ስትጣራ።
ባለፈው መታሰር ይብቃ
ላብ አደር በቃ ንቃ።
ያለም ግጽዋ ብሩህ ይሁን፣
ኢምንት ነን
እልፍ እንሁን
ኣዝማች
ዓልም አቀፍ ትግላችን ዛሬ ነው ታገሉ
ነገማ ብርሃን ነው ለሰው ልጆች በሙሉ (2 ጊዜ)
ሥርአትና ወጉ ግፋኛ
አዳይ ህግ፣ ሌባ ዳኛ
በቃ ይውደሙ ይደምሰሱ
ላዲሱ ቀን ተነሱ
ፍቅር ሰላም እንዲስፋፋ፣
ባዲስ ዓለም ባዲስ ተስፋ
ላብ አደር ተነሳ ተሰለፍ
ዳር እስከዳር ዓለም አቀፍ
አዝማች
ዓልም አቀፍ ትግላችን ዛሬ ነው ታገሉ
ነገማ ብርሃን ነው ለሰው ልጆች በሙሉ (2 ጊዜ)
ትርጉም፣ ነገደ ጎበዜ
ትግላችን፣ ቁጥር 1 ጥቅምት 1967
በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተመሪዎች ማህበር ወርሃዊ መጽሄት
Traditional songs lyrics collection
ባህላዊ የዘፈን ግጥም ስብስብ።
ሀረር ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉ ሸዋ
ልታንከራትተኝ አሸዋ ለአሸዋ
ሸዋ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ መንዝ
ከኛ ከጠንቀኞች ጦር ልታማዝዝ
መንዝ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ወሎ
አይኗ የሚመስለው የብረት አለሎ
ወሎ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ደስ
ሳዱላዋን ገጥማ ሆናለች ፈሰሴ
ደሴ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ጎንደር
ይመልከተው አንጂ አምላክ ፈጣሪ እግዜር
ጎንደር ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉ ትግሬ
እከተላታለሁ በለመደው እግሬ
ትግሬ ላይ ባስጠይቅ ናት አሉኝ መቀሌ
እከተላታለሁ እኔው እንደ አመሌ
መቀሌ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ የጁ
ይዟታል ወረሴ በማሩም በጠጁ
የጁ ላይ ባስጠይቅ ናት አሉኝ ዉርጌሳ
አገሬን ለቀኩኝ በሷ የተነሳ
ውርጌሳ ባስጠይቅ ገባች አሉ አምባሰል
የዳገቱ ክፋት ጠቆርኩ እንደ ከሰል
አምባሰል ባስጠይቅ ነች አሱኝ አልብኮ
ከመንገሻ አቦየ ልታጣላኝ አኮ
አልብኮ ባስጠይቅ ናት አሉኝ ርቄ
እከተላታለሁ ንብረቴን ለቅቄ
ርቄ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ቦሩ
እናቲቱ ናቸው ይህን የሚሰሩ
ቦሩ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉ ቃሉ
እንኳን ሂዳላቸው ደርሰው ይቃማሉ
ቃሉ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ አውሳ
እያደር ገነነች እንኳን ልትረሳ
አውሳ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ አሰብ
ያቺ ልጅ ተገኘች ጎረቤት ተሰበሰብ
አሰብ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ሰማይ
የት እመለሳለሁ መድረሻዋን ሳላይ
ሰማይ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ጎጃም
አንግዲህስ በቃኝ ነገር አላዓዛም
ጎጃሞች ካገኟት መቼ ይለቋታል
በማርሩም በጠጁም እዛው ያለምዷታል።
ሀረር ድሬ ደዋ ጂቡቲ ድንበር
እኔና አንቺ ሆነን ሶስተኛው እግዜር
ምን ብለሽኝ ነበር ምን ብየሸ ነበር?
ሀብት ያለው ገና ሃብት የሌለኝ ቆሜ
አጥርሻን ጨረስኩት ቆርጥሜ ቆርጥሜ
ሁለቱንም አይኔን ዳመና ጣለበት
ብዙ ነገር አይቷል ይጥፋ ምናለበት
ሁልጊዜ ጎፈሬ ተበጥሮ ኑሮ
ላኪልኝ መቀሱን ቁርጥ ነው ዘንድሮ
ሂዱ ሂዱ ይላል ብረሩ ብረሩ
አንድ የሚወዱት ሰው ሲጠፋ ካገሩ
ሂጂልኝ ወድያልኝ ፍቅርሽ መላም የለው
ጊዜ ለሰጠው ሰው ታደያለሽ ምነው?
ሃሜተኛም ይሣ ለዋሽም ይለውስ
እጅዋን በጄ ይዤ እጮሃለሁ ለንጉስ
ሃምሌ ነሃሴ መጣ ሁለት ወር ክረምት
ለልቤ ማረፊያ ቤት ሳልሰራለት
ሃምሌ ነሃሴ መጣ ስሩ ደነደነ
የወር ቀለብ የለኝ ቤቴ አልተከደነ
ሃምሌ ድንጋይ ይዟል ሰው ሲገልላችሁ
ነሃሴ ጦር መዛል ሰው ሊገላላችሁ
አትገላግሉም ወይ ያላችሁ ያላችሁ?
ህመሜ በሰው ፊት እንዳታዋርደኝ
እኔኑ ብቻየን ጉስም ጉስም አርገኝ
ሆዴ እንደመንደዱ ፍምም አልወረደው
እህል እየበላ ውሃ አያበረደው
ሆዴ እየነደደ ቢሸተው እንጀቴ
ስጋ ጠብሷል ብሎ አማኝ ጎረቤቴ
ሆዴ እየነደደ ጥርሴ እየመለሰው
አሁን በጎ አዳሪ እመስላለሁ ለሰው
ሆዴን ባርባር አለው ወልዶ እንደቀበረ
ተዋዶ መለየት በኔ አልተጀመረ