አጭር የህይወት ታሪክ

"እድሜዬ ሃያ ፣ የስራ ልምዴ ስልሳ

አጭር የህይወት ታሪክ

"እድሜዬ ሃያ ነው፣ የስልሳ አመት ልምድም አለኝ"

ነገደ በጥቅምት 2016 ሰማንያኛ የልደት በአሉን ሲያከብር የተናገረው ቃል ነው። ከእነዚህ የስልሳ አመታት ልምዶች ወስጥ በዋናነት ቦታ የያዘው ለማህበራዊ ፍትህ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለብሄራዊ ነፃነት፣ ለፖለቲካ ብዝሃነት፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረትና የኢትዮጵያ ህዝቦች በመከባበር፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት ለሚኖሩባት አገር መርህዎችን መሰረት በማድረግ በጽኑ ሲሞግት የተጓዘባቸው አመታት ናቸው ።

ልጅ ገጣሚ

ትንሽ የሚገርመው ግን፣ በወጣትነቱ ዘመን ከፖለቲካ ይልቅ ወደ ግጥም ደራሲነት የሚያመዝን ዝንባሌ እንደነበረው ስንረዳ ነው። ገና የአስራ አንድ አመት ልጅ ሆኖ፣ ንጉሱ በ1946 ዓም አሜሪካንን ጎብኝተው ወደ አገር ሲመለሱ፣ አድናቆት በተሞላው መንፈስ፣ እንኳን ደህና መጡ በሚል ርእስ የመጀመሪያውን ግጥም ጻፈ። ግጥሙ፣ ስሙ ሳይጠቀስ ፣ ከደሴ ከተማ በአስራ አንድ አመት ወጣት የተጻፈ ተብሎ በመንግስት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጣ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ተማሪም ሆኖ የፖለቲካ ነገር ብዙም ልቡ ውስጥ አልገባም ። ወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ፣ የአፄ ሃይለ ሥላሴን መንግስት በህዝቦች መሃከል የኢኮኖሚ ብዝበዛንና ድህነትን አስፋፋ በማለት ድምጻቸውን ማስተጋባት የጀመሩበት ቢሆንም፣ ነገደ በዚህ እንቅስቃሴ አለተሳተፈም። ለምሳሌ በአመታዊው የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የግጥም ውድድር ላይ፣ በወቅቱ የተማሪውን ንቃት ለመቀስቀስ እነ ታምሩ ፈይሳ፣ ዩሃንስ አድማሱ፣ ኃይሉ ገብረ ዮሃንስ (ገሞራው)… ወዘተ ፖለቲካ ይዘት ያላቸው ግጥሞች ሲደረድሩ፣ እሱ ግን ለውድድሩ ያቀረበውና አንደኛ ሆኖ የተሸለመበት ግጥም “አጉል ቦታ አምሽቼ’’ የሚል ነው። አንድ ሽማግሌ አባት አንድ ልጃቸው ያዘጋጀው ፓርቲ ላይ ተገኝተው በዚህ ‘ፓርቲ’ በሚሉት ዘመን አመጣሽ ክስተት ላይ ያላቸውን ወግ አጥባቂና የተቃውሞ ሃሳብ እንደ ቀልድ እያደረገ የሚያንጸባርቅ ግጥም ነበር።

የፖለቲካ ንቃት

ቀስ በቀስ ወደ ፖለቲካው አለም የተቀላቀለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ለመቀጠል ፈረንሳይ አገር፣ ኤክስ አን ፕሮቫንስ (Aix-en-Provence ) ከተማ ከደርሰ ጥቂት አመታት ብኋላ ነው። በመጀመሪያ ሁለት አመታት የፈረንሳይ ተማሪነት ዘመኑ ፖለቲካው ውስጥ ብዙ ሳይገባ ቆየ። አውሮፓ በደረሰበት አመት፣ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተመሪዎች ማህበር (አኢተማ) ከተቋቋመ ገና አራት አመቱ ሲሆን፣ በአመታዊ ጉባኤዎቹ ያስተጋባ የነበረው አቋም ስለሃገሪቱ ልማት ገንቢ ሃሳቦችን ለንጉሰ ነገስቱ መንግስት በመሰንዘር የተወሰነ ነበር፡፡ አላማውም በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ይገኙ የነበሩ ተማሪዎች የሃገሪቱ እድገት የሚፋጠንበትን ዘዴና ለሃገሪቱ ይጠቅማሉ በሚሉዋቸው ሀሳቦች ላይ መወያየት ነበር።

በግሬጎርያን አቆጣጠር የስልሳዎቹ መጀመሪያ አመታት የማህበሩ አርማ ላይ ‘በቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ የበላይ ጠባቂነት’ የሚል ሃረግ ነበረበት፡፡ አመታዊ ጉባኤዎች ሲካሄዱም የተሳታፊዎች መጓጓዣ ወጭም ሆነ በስብሰባ በሚቆዩበት ጊዜ፣ የመኝታም ሆነ የምግብ ወጭያቸው የሚሸፈነው ከትምህርት ሚኒስቴር በሚላክ ገንዘብ ነበር፡፡

በ1956 ዓም ቪየና በተክሄደው ጉባኤ ላይ፣ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር የማርክሲዝምን ርዕዮተ አለም በመቀበል ፊውዳሊዝምን፣ የንጉሰነገስቱን አገዛዝና ኢምፔረያሊዝምን የሚቃወም አቋም ይዞ ወጣ። በንጉሱና በተማሪዎች መሃከል ጨርሶ መቆራረጥ ተከሰተ። እዚህ ላይ ልብ መደረግ ያለበት ነገር፣ በአለም አቀፍ ደረጃ በኩባ አብዮትና በቪየትናም ጦርነቶች ሳቢያ ፣በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓና ኤሽያ የአለም ወጣቶች በነዚህ ጦርነቶች ዙሪያ ከፍተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ወቅት ነበር። የኢትዮጵያንም ተማሪዎች፣ በውጭም ሆነ በውስጥ ወደ ስር ነቀል ለውጥ ብሎም ወደ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ከመሯቸው ክስተቶች ዋናዎቹ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።

ነገደ ኤክስ አን ፕሮቫንስ ከደረሰ በሁዋላ መጀመሪያ ወደ ማርክሲዝም ፣በተለይም ወደ ትሮትስካይት የፖለቲካ መስመር የመጣው ክፈረንሳውያን ጓደኞቹ ጋር በነበረው ግንኙነት አማካይነት ነበር። ከቪየና ጉባኤ በኋላ በተከተሉት አመታት የአዎሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበርን በመቀላቀል፣ በፈረንሳይ፣ በአውሮፓም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ የአመራር ቦታዎች የያዘበት አመታት ነበሩ።

  • ከታህሣስ 1959 ዓም – 1960 ዓም ድረስ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ሊቀ መንበር
  • ከነሃሴ 1960- 1963 በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር የመጽሄት አዘጋጅ ቦርድ አባልና በ1963 የቦርዱ ሊቀመንበር
  • ከነሃሴ 1962 – 1963 በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዜዳንት
  • በነሃሴ 1960 የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መስራች አባል።

በኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎ

በ 1966 ዓም አብዮቱ ፈንድቶ ደርግ ስልጣን ይይዛል። እንደ ሌሎች ጓደኞቹ ነገደም በለውጡ ሂደት ለመሳተፍ ወደ አገር ይመለሳል። የህዝቡን ጥያቄዎች እውን ለማድረግ መኢሶን ከደርግ አንጻር ሂሳዊ ድጋፍ ይሚል አቁዋም ይይዛል። መሬት ላራሹ የሚለውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ዋና መፈክር ወደ ተግባር የሚያሸጋግር አዋጅ በ1967 ዓም ይታወጃል። ይህንን የብዙ ገበሬዎችን ህይወት የቀየረ አዋጅ በስራ ላይ እንዲውል ለማድረግ፣መኢሶን ያለውን ሃይል በሙሉ ለዚህ መሳካት ያንቀሳቀሳል።

በሚያዝያ 1968 ዓም በታወጀው በብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም መሰረት፣ ከሚያዝያ 1968 እስከ ነሐሴ 1969 ባለው ጊዜ ውስጥ በመኢሶንና በደርግ መሃከል ይፋ የትብብር ዘመን ይፈጠራል። ፕሮግራሙን በስራ ላይ ለማዋል፣ የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት ይቁዋቁዋማል። ነገደ የዚህ ጽህፈት ቤት አባልና በወር ሁለቴ የሚታተመው “አብዮታዊት ኢትዮጵያ” መጽሄት ዋና አዘጋጅ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ የዴሞክራሲያዊ መብቶች አዋጅ እንዲያዘጋጅ ሃላፊነት ይሰጠዋል። ነገር ግን የተረቀቀውን አዋጅ ለመቀበል ደርግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ በደርግና በመኢሶን መካከል ዋነኛው የልዩነት ነጥብ ይሆናል። በዚህም የተነሳ ሁለቱ ወገኖች አብረው መቀጠል የማይችሉበት ሁኔታ በመፈጠሩ መኢሶን በነሃሴ 1969 ዓም ሂሳዊ ድጋፉን በማንሳት ወደ ተቃውሞ ይገባል።

በተከተሉት ወራቶች፣ የፖለቲካ ግድያዎችና እስራቶች በመኢሶን አባላትና በሌሎች ተራማጅ ሀይሎች ላይ እየተሳፋፉ ይሄዳሉ። በወቅቱ ውጭ አገር የነበረው ነገደ ከዚህ ለማህበራዊ ፍትህና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ከተሰዉት ትውልድ ከተረፉት ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው። በዚህ በጓዶቹ መስዋዕትነት በጣም የተነካው ነገደ፣ ጥልቅ ሃዝኑን ለመግልጽ እንደገና ወደ ግጥም ባህሉ በመመለስ “በይ ብእሬ” በሚል ርእስ ገጠመ። “በይ ብዕሬ ግጠሚ፤ አትች ተች፣ እኝኝ በይ ወትውች። በይ ተዋጊ ብእሬ፣ ብቻ ! ለእውነት ለፍትህ ሙቺ። ለእውነት በእውነት ቆመሸ፣ ለፍትህ ለነፃነት ለህዝብ ብለሸ፣ ተናገሪ ! ወዳጅ እንዲሰማ አርገሽ ፣ ተዋጊ ! ………።” በማለት ያለ አንዳች ፍርሃት በአቁዋም ጽንቶ መቆም እንደሚያስፈልግ ይተቻል።

የስደት ዘመን

ከ1969 ዓም ጀምሮ፣ በስደት መኖር በጀመረበት በፈረንሳይ አገር ፣ በአገሪቱ ውስጥ የተደላደለውን አምባገነንነት ለመዋጋት የተለያዩ ሃሳቦችን በማፍለቅ፣ የተለያዩ ድርጅቶችን ፈረንሳይ አገር አቋቁሟል ።

  • በ1971 ዓም “በኢትዮጵያ ለጭቆና ሰለባዎች የድጋፍ ኮሚቴ” በሚልና በኋላ “ለኢትዮጵያ የድጋፍ ኮሚቴ” ወደሚል የተቀየረውን ድርጅት፣
  • በ1982ዓም “በኢትዮጵያና አፍሪካ ቀንድ የምርምርና የተግባር ኮሚቴ በፈረንሳይኛ (Groupe de Recherche et d’Action pour la Paix en Ethiopie et dans la Corne de l’Afrique (GRAPECA)) የተባለ ድርጅት መሰረተ/ተመሰረተ። አላማው ሰላም እንዲሰፍን፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እና። ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍን ማበረታታት ነበር። ለዚህም፣ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን እና የፖለቲካ ድርጅቶችን በማሰባሰብ ሰላማዊ የዲሞክራሲያዊ ሽግግር አማራጭ ለማቅረብ የሚመክር የውይይት መድረክ በመፍጠር ሶስት ትልልቅ ኮንፈረንሶች አዘጋጅተዋል። እነዚህም
  • በ1983 ዓም ፣ ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከአምባገነንነት ወደ ዲሞክራሲ – የሽግግር ወቅት ችግሮች በሚል የተለያዩ አስተሳሰብ ያላቸውን የኢትዮጵያ ምሁራን ያሳተፈ ክንፈራንስ፣
  • በማርች 1985 የሰላምና እርቅ አገር አቀፍ ጉባኤ ለማዘጋጀት በፓሪስ ከተማ የተካሄደውና ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉበት ስብሰባ ሲሆን፣ የስብሰባው አላማ ኢህአዴግን ጨምሮ በሃገሪቱ ያሉት የፖለቲካ ሃይሎች አንድ ሰፊ ብሄራዊ የእርቅና የሰላም ጉባኤ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነበር። ቀጥሎም ከአስር ወር በሁዋላ በታህሳስ ወር 1985 ዓም አዲስ አበባ የሰላምና እርቅ ጉባኤ አካሄደ።
  • በ1990 ዓም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች ህብረት (ኢተፖድህ) የተቋቋዋመበት ሲሆን፣ አላማውም የተቃዋሚ ሃይሎች የትግል ትብብር የሚያጠናክርበትን ስልት ለመቀየስ ነበር።

የሰላምና የውይይት ባህልን ለማዳበር GRAPECA፣ ራዲዮ ሰላም እና ከዚያም ቀስተ ዳመና ራዲዮ የሚባሉ ነፃ ሬዲዮ ጣቢያዎች አቋቋመ። የሁለቱም ራድዮኖች አላማ ወደ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ በሰላማዊ መንገድ የመሸጋገርን አስፈላጊነት አጉልቶ ለማሳየት ውይይቶችን ማበረትታት፣ ሰብአዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ ሰላም፣ የአብሮ መኖር እሴቶች እንዲዳብሩ ማገዝ ነበር። ለዚህም የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ባለ ብዙ ገጽታ

የነገደ ህይወት በፖለቲካ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሙዚቃ በጣም ይወዳል። ክራርና ሃርሞኒካም ይጫወታል። ባህላዊ የዘፈን ግጥሞችን መሰብሰብ ከሚወዳቸው ነገሮች አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ሽህ የሚጠጉ የባህላዊ ግጥም ስብስቦች አሉት።

ነገደ ጨዋታ ያውቃል። ሁኔታዎችን በተረትና ምሳሌ መግልጽ ይሆንለታል። ሌላ ተስጥኦው በሚሰጣቸው የመልስ ዘይቤ የታወቀ ነው። ምን ይል ይሆን ተብሎ ይጠበቃል። ከነዚህ መሃከል ለምሳሌ ያህል ፣ በ1966 አም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስትና የታንዛንያ ሪፐብሊክ ህገ መንግስታት የሚያነጻጽር የዶክትሬት ቲስሱን ባቀረበበት ወቅት፣ አንዱ ፕሮፌሰር ላቀረቡበት ሂሳዊ አስተያየት የሰጠው መልስ ነው። በ1966 ዓም፣ ከ60 የሚበልጡ የሃይለ ሥላሤ መንግስት ባለስልጣናት ይረሸናሉ። ያቀረበውን ቲስስ ሲተነትን ግን፣ ነገደ እነዚህ ሰዎች መረሸናቸውን ሳያወሳ ያስረዳል። በስፍራው ከነበሩት ፕሮፌሰሮች አንዱ  “እነዚህ ሰዎች ከወር በፊት መረሸናቸውን ሳታወሳ ስለነሱ አሁንም በህይወት እንዳሉ ትናገራለህ’’ የሚል ሂስ ይቀርብበታል። ለዚህም ነገደ ‘’ፕሮፌሰር ይስሙኝ እኔ እያቀረብኩ ያለሁት የዶክትሬት ቲሲስ እንጂ እለታዊ ጋዜጣ አይደለም።’’  ብሎ ይመልሳል።

ነገደ በጽሑፎቹ፣ በቃለ ምልልሶቹ እና በአቋሞቹ ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና በተከታታይ ስልጣን ላይ ስለወጡት መሪዎች ዘመን፣ ስለ አገሪቷ የፖለቲካ ሂደቶች እንዲሁም ስለ ግል ዝንባሌውና የፖለቲካ አቋም ይዞን ይጓዛል።

ቤተሰቦቹ

ሃምሌ  2017

የጊዜ ሂደት

ጥቅምት 6 ቀን 1936 ደሴ ተወልደ። ነገደ ዊንጌት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በ1949 ዓ/ም አዲስ አበባ እስከመጣ ድረስ ያደገው ወሎ ነው። አባቱ አቶ ጎበዜ ጣፈጠ የወሎ፣ የትግራይና የበጌምድር ትምሀርት ቤቶች ሥር አስኪያጅ ነበሩ። መሰረተ ትምህርት ስለሚስፋፋበት ሁኔታ አቶ ጎበዜ ለንጉሱና ለትምህርት ሚኒስቴር ጥናት አቅርበው፣ ሃሳባቸው ስለ ተደገፈ በ1951 ዓ/ም የመሰረተ ትምህርት ዲሬክተር ሆነው በ 1951 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ ሲዛወሩ፣ የቤተሰቡ ኑሮ አዲስ አበባ ሆነ። እናቱ ወ/በላይነሽ እጅጉ ይባላሉ።

እናትና አባቱ የተገናኙት በንግስት ዘውዲቱ ሃኪም ቤት፣ ወይዘሮ በላይነሽ በአስታማሚነት፣ አቶ ጎበዜ ለሃኪሞች በአስተርጓሚነት ተቀጥረው በሚሰሩበት ጊዜ ነበር። ትዳር መስርተው ዘጠኝ ልጆች አፍርተዋል። ነገደ የቤተሰቡ ሶስተኛ ልጅ ነው። አቶ ጎበዜ ትምህርት ማስፋፋትን የህይወታቸው ዋና አላማ አድርገው የያዙ ሰው ነበሩ። ልጆቻቸውን በእረፍት ጊዜ አስተማሪ ቀጥርው ያሰተምራሉ። አንድ ጊዜ ለጆቻቸውን እንግሊዘኛችሁ እንዲሻሻል እርስ በራሳችሁ በእንግሊዘኛ እንድትነጋገሩ ብለው ያዛሉ። ከልጆቹ አንዷ፣ እንግዲህ በቤቱ ውስጥ ጠቅላላ ኩርፊያ ሊሆን ነዋ ብላ መለሰች ይባላል። በአዛውንት እድሜያቸውም የልጅ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ሲዘጋ ያስጠኑ ነበር።

1942-1947/48 ዓ/ም ወይዘሮ ስሂን ት/ቤት፣ ደሴ ተማረ። ከአራተኛ ወደ ስድስተኛ ክፍል ዘሏል። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳይጨርስ መምህር አካለ ወልድ ትምሀርት ቤት ደሴ ተከፈተ። ትምሀርት ቤቱ በቂ ተማሪ ስላልነበረው ከወይዘሮ ስሂን ስድስተኛ ክፍል ከነበሩትና ጥሩ ውጤት ካመጡት መሃከል አንዳንድ ተማሪዎች ሰባተኛ ክፍል ዘለው አዲሱ ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍል እንዲገቡ ተወስኖ ነገደም ወደዚያው ሄደ።

1949-1952 ዓ/ም ጄኔራል ዊንጌት አዲስ አበባ ትምህርቱን ቀጠለ። ነገደ ዊንጌት ሲደርስ ገና የአስራ ሶስት አመት ልጅ ነበር፡፡ በወቅቱ የገና በዓል ሲደርስ ተማሪዎቹ ንጉሱ ፊት እየቀረቡ የገና ስጦታ ይቀበሉ ነበር፡፡ ነገደ ተራው ደርሶ ንጉሱ ፊት ሲቀርብ፣ እሳቸውም በልጅነቱ ተገርመው ‘’ ደሞ አንተ እዚህ ምን ትሰራለህ?’’ የሚል ጥያቄ አቀረቡለት፡፡ እሱም ‘’ግርማዊ ሆይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቅቄና ፈተናውን አልፌ መጣሁ፡፡’’ ብሎ ይመልሳል፡፡

1953-1956 ዓ/ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ነበር። መጀመሪያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንደገባ መማር ይፈልግ የነበረው የህክምና ትምህርት ጀመረ፡፡ ሶስት ሳምንት ያህል ብቻ ሳይንስ ፋኩልቲ ከቆየ በኋላ ጨርሶ ስላልተስማማው ቀይሮ እስከ ቢኤ ዲግሪውን ወደ ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ አመራ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ አልነበረም።

ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ አመት ተማሪ ሆኖ የሶስተኛ አመት ትምህርቱን አሜሪካ በስኮላርሽፕ መከታተል የሚችልበት ሁኔታ ተከሰተ፡፡ በወቅቱ አሜሪካኖች Foreign Students Leadership Project (FOSLEP) የሚባል ፕሮግራም ነበራቸው፡፡ ይህ ፕሮግራም ከሶስተኛው አለም በተለይም ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሶስተኛ አመት ትምህርታቸውን አሜሪካ ሄደው የሚከታተሉበትና ከዚያም ተመልሰው በቀድሞ ዩኒቨርሲቲያቸው ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የተማሪ ንቅናቄዎች ውስጥ በአመራር ደረጃ እንዲሳተፉ የሚያመቻቸው ፕሮግራም ነበር፡፡ ሆኖም ፕሮግራሙ የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዜዳንት የነበሩትን ልጅ ካሳ ወልደማሪያምን ጨምሮ ባለስልጣናትን ያስቆጣ፣ በነሱ አስተያየት ራዲካል ግራ ሊባሉ የሚችሉ አቋሞች የያዙ ተማሪዎችን የሚያግዝ ፕሮግራም ነው ብለው ያስቡ ነበር። ከዚህም የተነሳ ልጅ ካሳ ወልደ ማሪያም ይህን ፕሮግራም የራዲካሎች መፈልፈያ አድርገው ስለቆጠሩት እንዳይቀጥል ወሰኑ፡፡ ነገደም ከሃገር እንዳይወጣና ወደ አሜሪካ ለመሄድ የሚያስፈልገውን ቪዛ እንዳይሰጠው ተወሰነ፡፡ ከዛም እዛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በቢኤ. ዲግሪ በኢኮኖሚ በ1956 ዓ/ም፣ ተመርቋል።

በ1957 ዓ/ም ወደ ፈረንሳይ የተጓዘው፣ ከፈረንስይ መንግስት በስኮላርሽፕ አግኝቶ ነበር። ከሌሎቹ አፍሪካውያን ስኮላርሽፕ ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለተማሪዎቹ ወርሃዊ ድጎማ ያደርግ ነበር። ከሌሎቹ የአፍሪካ ስኮላርሽፕ ተማሪዎች አንጻር የኢትዮጵያ ተማሪዎች በጣም የተሻለ የኑሮ ደረጃ ነበራቸው ማለት ይቻላል።

ነገደም የመጀመሪያ ዓመት የፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት ከተማረ በኋላ ህግ ፋኩልቲ ተመዝግቦ ትምህርቱን ቀጠለ። 1957-1967 ዓ/ም ኤክስ አን ፕሮቫንስ ቆይታ በኋላ በታህሳስ 1967 ዓ/ም በህግ የዶክተሬት ዲግሪ ተመረቋል።

  • ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ከተመረቀ በኋላ፣ ለሶስት ወራት ገንዘብ ሚኒስቴር ሰርቷል።
  • በትምህርት ዘመን ላይ እያለ በጎን አንዳንድ ስራ በመስራት፣ ነገደ ተጨማሪ ገቢ ነበረው በዩኒቨርሱቲው መጽሃፍት ቤት በረዳትነት ሰርቷል።
  • የዶክትሬት ቲሲሱን በሚሰያናዳበት ወቅት ደግሞ ኢንስቲትዩት ፎር አሜሪካን ዩኒቨርሲቲስ በተባለ ተቋም፣ ፈረንሳይኛ እየተማሩ እዛው በዛው ሶስተኛ አመት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ፈረንሳይ አገር ለሚመጡ አሜሪካዊ ተማሪዎች ‘የአፍሪካ ፖለቲካል ኢንስቲቱሽንስ’ በሚል ርእስ አስተማሪነት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። በዚያን ጊዜ፣ በኤክስ አን ፕሮቫንስ የተማሪዎች ልምድ፣ የፖለቲካ ጥናት ክበቦችም ሆኑ ሌሎች ስብሰባዎች የሚደረጉት በየቡና ቤቶች ውስጥ በነበሩት ልዩ የመሰብሰቢያ ክፍሎች ውስጥ ነበር፡፡ እሱም ተማሪዎቹን ወደ እነዚህ የቡና ቤቶች መሰብሰቢያ ክፍሎች እየወሰደ በራሱ ወጭ እየጋበዘ ያስተምር ነበር፡፡

የፖለቲካ ተሳትፎን በተመለከተ በተለይም ከ1956 ዓ/ም የቪየና ጉባኤ በኋላ ነገደ ቀስ በቀስ በማህበሩ ውስጥ የሚያደርገው ተሳትፎ እየጨመረ መጣ፡፡ ከነሃሴ 1960 ዓ/ም አንስቶ እስከ ነሃሴ 1963 ዓ/ም ድረስ ለሶስት አመታት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር የመጽሄት አዘጋጅ ቦርድ አባልና እንዲያውም በ1963 ዓ/ም የቦርዱ ሊቀመንበር ሆኖ የማህበሩን መጽሄቶች ታጠቅ፣ ትግልችንንና ትግላችን ዜናን የማዘጋጀቱን ሃላፊነት ወስዷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከነሃሴ 1962 ዓ/ም እስከ ነሃሴ 1963 ዓ/ም ድረስ የአውሮፓው ማህበር ፕሬዜዳንትነት ተመርጦ እያለ እዛው በዛው ደግሞ እስከ ሰኔ 1964 ዓ/ም ድረስ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ አፍሪካና ቅርብ ምስራቅ የሚገኙ ማህበራትን ያሰባሰበው አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዜዳንት ሆኖ አገልግሏል

  • የካቲት 1967 አዲስ አበባ ተመለሰ
  • አለም አቀፍ አሳታሚ ድርጅት መስራችና የድርጅቱ ፕሬዜዳንት (ሰኔ 1967ዓ/ም - ነሃሴ 1969 ዓ/ም)
  • ከደርግ ጋር ትብብር - የአብዮቱን ሂደት መስመር ለማስያዝ፣ ህዝባዊ ሃይሎች - በገበሬ፣ በሰራተኛ፣ በከተማ ነዋሪዎች፣ በወጣቶችና በሴቶች ማህበር እንዲደራጁ ለማገዝ የተቋቋመው የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት አባልና በዚህ ድርጅት ውስጥ የኢንፎርሜሽንና የፖለቲካ ትምህርት ኮሚቴ ፕሬዜዳንት ሆኖ ሰርቷል (ታህሳስ 1967ዓ/ም - ነሃሴ 1969 ዓ/ም) ፡፡ በዚህ ኮሚቴ ስር ከአከናወናቸው ተግባራት፣
    •  የካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት ምስረታና ክትትል
    •  በህዝብ ድርጅት የማስታወቂያና የፍልስፍና ማስፋፊያ ኮሚቴ ሃላፊና በወር ሁለት ጊዜ ይታተም የነበረው አብዮታዊት ኢትዮጵያ መጽሄት ዋና አዘጋጅ
    •  የኢትዮጽያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ህብረት ለማቋቋም ተሳትፎ
  • በነሃሴ 1969 ዓ/ም መኢሶን ከደርግ ጋር ግንኙነቱን አቋርጦ ህቡእ ሲገባ፣ ስዊስ አገር ሎዛን ከተማ በተካሄደው በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር 17ኛ ጉባኤ ሊሳተፍ ወጥቶ ስለነበረ፣ ቀደም ሲል ከድርጅቱ አመራር ጋር በተደረገ ስምምነት መሰረት በዛው እንዲቀር ተደረገ፡፡ ከዛም በውጭ አገር የመኢሶን አመራር አባልና የድርጅቱ የውጪ ተወካይ ሆኖ መስራት ጀመረ።
  • መስከረም 1970- ሚያዝያ 1970 ዓ/ም : በኩባና በየመን መሪዎች ግብዣ የመንና ኩባ ቆይታ አደረገ። የእነዚሁ አገሮች መሪዎች፣ ከኮለኔል መንግስቱ ጋር ውይይት እንዲካሄድ ባቀረቡት ይልተሳካ ሃሳብ መሰረት አዲስ አበባ ሁለት ወር ኩባ ኤንባሲ ቆየ።
  • በ1972 ዓ/ም ከኢትዮጵያ ጋር አነድነት ከሚቴ (Comité de Solidarité avec l’Ethiopie COSETH) በፈረንሳይ አገር የተመዘገበ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መስራችና ሊቀመንበር
  • በ1982 ዓ/ም የሰላም ለኢትዮጵያና አፍሪካ ቀንድ የምርምርና የተግባር ቡድን - Research and Action Group for Peace in Ethiopia and the Horn of Africa (GRAPECA, known by its French acronym), መስራችና ዋና ዲሬክተር። በዚህ ድርጅት ስር ከተከናወኑት ስራዎች ዋና ዋናዎቹ፣
    • በሃምሌ ወር 1983 ዓ/ም « ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከአንባ ገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ » በሚል ርእስ የፓሪስ ስብሰባ አዘጋጅ፣
    •  የሰላምና እርቅ በኢትዮጵያ አገር አቀፍ ጉባኤ» ከታህሳስ 9 እስከ 13 1986 ዓ/ም ዓ/ም በአዲስ አበባ ለተክሄደው ስብሰባ የአዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀ መንበር፡፡
    • በGRAPECA የሚዘጋጅ፡Addis Digest የተባለ መጽሄት ዋና አዘጋጅ። (1987/1989 ዓ/ም)
    • የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት (ኢተፖድህ) ስብሰባ አዘጋጅ 1990 ዓ/ም
    • ቀስተ ደመና ሬድዮ መስራችና ዋና ዲሬክተር (1990-1995 ዓ/ም)
  • መኢሶንን በመወከል፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት አመራር አባል (1982ዓ/ም )
  • የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት - ኢተፖድህ ሊቀ መንበር (1990ዓ/ም)

Privacy Preference Center